ብዙ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን ችግራችን አንድ ያለመሆን ነው፤ ልዩነቶቻችንን ትተን አንድ እንሁን፤ አንድነት ኃይል ነው ወዘተ እያልን ጩኸናል፤ አስተምረናል፤ ጽፈናል፤ አንብበናል፤ አዚመናል፤ ሰብከናል፡፡ አሁን አሁን ግን ሳስበው እንዲያውም ችግራችን አንድ ከመሆን የመጣ ነው የሚመስለኝ፡፡ እንዲያውም ሀገራችንን አሁን ለደረሰችበት ውድቀት የዳረጋት አንድ መሆናችን ነው፡፡ ደግሞ መች ተለያይተን እናውቃለን? መች ልዩነት አለ በመካከላችን? ሁላችንም እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ አንድ አይደለን እንዴ፡፡
ለመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን የተለያየነው በምን በምንድን ነው? በዘር? በሃይማኖት? በፖለቲካ? በአመለካከት? በምንም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የሚሠራው ፊልም አንድ ዓይነት ነው፡፡ ተዋንያኑ ግን በየጊዜው ይለያያሉ፡፡ ፊልሙ የሚሠራበት ቦታ እና ቋንቋ ግን ይለያያል፡፡ አንዳንዶቹ ያንኑ ፊልም በሚገባ ይሠሩታል፤ ይዋጣላቸዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ፊልሙን በበቂ ሁኔታ አይተውኑትም፡፡ በዚያም ተባለ በዚህ ግን በፊልሙ አንድ ነን፡፡ በፊልሙ ውስጥ መገዳደል፤ መጨራረስ፣ አምባገነንነት፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን፣ጠባብነት፣ ጎጠኛነት ወዘተ አሉበት፡፡
ፊልሙ በአማርኛም ተሠራ በኦሮምኛ፤ በትግርኛም ተሠራ በሶማልኛ፤ በአፋርኛም ተሠራ በወላይትኛ፣ በሐረሪኛም ተሠራ በሲዳምኛ የፊልሙ ስክሪፕት ያው ነው፡፡ የማጀቢያ ዜማውም «ኧረ ጎራው ኧረ ደኑ፤ ግደል ግደል አለኝ፤ የሚቃወምህን አጥፋው አጥፋው አለኝ፤ ካንተ ሌላ ሃሳብ አትስማ አትስማ አለኝ´፤ የሚለው የጥንቱ ዘፈን ነው፡፡
ታድያ ኢትዮጵያውያን አንድ ዓይነት ፊልም እየሠሩ እንዴት ነው የሚለያዩት? ኧረ አንድ ናቸው፡፡
ለመሆኑ የዘር ልዩነት አለን እንዴ? ሁላችንም ከምናውቃት ቋንቋ በላይ መስማት አንፈልግም፤ ስለሌላው ዘር የሚያንቋሽሹ ቃላት በሁላችንም መዝገበ ቃላት ውስጥ አሉ፤ የተናቁ እና የተዋረዱ ማኅበረሰቦች በየዘራችን አሉ፤ ገድለን ጀግና የምንሆንባቸው ማኅበረሰቦች በየጎሳችን አሉ፤ ሁላችንም ጎሳዎቻችንን ብቻ የሚወክሉ ፓርቲዎች አሉን፤ ሁላችንም ጎሳዎቻችንን ነጻ ለማውጣት እንታገላለን፤ ሁላችንም ተጨቁነናል፤ ታድያ አሁን እኛ በዘር ተለያይተናል? ምኑ ላይ ነው ልዩነታችን? አንድ ዘር እኮ ነን፡፡
አሁን እኛ በፖለቲካ ተለያይተናል? ለመሆኑ ምንድን ነው የለያየን? ሁላችንም «ሌላ ድምፅ አልሰማም ከንግዲህ በኋላ´ አይደል እንዴ የምንለው፡፡ የገዥ ፓርቲ መሪዎችም አይለወጡም፤ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም አይቀየሩም፤ ፖሊት ቢሮ፤ ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ጠቅላላ ጉባኤ፤ በሁሉም ዘንድ አሉ፤ ለምሳሌ በቅርቡ በአምስተርዳም የአቶ መለስ ዜናዊ ምስል ያለበትን ቲሸርት የለበሰ ሰው በኢትዮጵያውያን መደብ ደቡ እንደ ትልቅ የድል ዜና ሲነገር ነበር፡፡ ታድያ ገዥው ፓርቲ እኛን ከዚህ እና ከዚያ ከለከለን ብሎ መናገር እንዴት ይቻላል? ልዩነታችንስ ከምኑ ላይ ነው? እኔ ልሙት አንድ ነን፡፡
እዚያ ኢሳት ተከለከለ ብለን ሰልፍ እንወጣለን፤ እዚህ የእነ እገሌን ሬዲዮ አትስማ፤ ቴሌቭዥናቸውን አትይ፣ እንጀራቸውን አትግዛ እንላለን፤ እዚያ 99 በመቶ የሚያሸንፍ አለ፤ እዚህም 99 በመቶ የሚያሸንፍ አለ፡፡ ሁሉም ተቃራኒ ሳይሆን ጠላት አለው፡፡ ሁሉም ጠላቱን ለማውደም ተነሥቷል፡፡ አሁንም «እገሌ ያሸንፋል´ ብለን እንፎክራለን፡፡ ታድያ በምንድን ነው ልዩነታችን? ኧረ አንድ ነን፡፡
ማነው ለመሆኑ ይኼ ኢትዮጵያውያን ተለያይተዋል እያለ የሚያሟርትብን፡፡ ባያውቀን ነው እንጂ እኛስ ተለያይተን አናውቅም፡፡ አሁን እኛ ተለያይተናል? ስንት ሰው አለ እባካችሁ ያላየውን የሚያወራ፡፡
በውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ገለልተኛ፣ ስደተኛ፣ የሀገር ቤት እያሉ ተለያይተዋል ብሎ የሚያማን ሰው ምን የተረገመ ነው፡፡ አሁን በኛ መካከል እንዲህ ያለ ልዩነት አለ? ሁሉም ጳጳስ ይፈልጋሉ፤ ሁሉም ግን በጳጳስ መታዘዝ አይፈልጉም፡፡ ሁሉም በስም የተለያዩ መስለው ለመንግሥት ባስገቡት ደንብ ግን አንድ ናቸው፡፡ ሁሉም የተለያየ ስም ነገር ግን አንድ ዓይነት ግብር ያለው ቦርድ አላቸው፡፡ ሁሉም ዋናው ገቢው ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ሁሉም ጋ የሚፈልጡ የሚቆርጡ ወይዛዝርት፤ የሚያዝዙ የሚናዝዙ መኳንንት፤ የሚከታተሉ የሚቆጣጠሩ ፖለቲከኞች፤ የሚፈሩ፣ ለሥጋ የሚያድሩ አገልጋዮች፤ አሉ፡፡ ታድያ በምን ተለያይተን ነው ተለያዩ እያሉ የሚያሟርቱብን፡፡
ለእነዚህ ገብርኤል የጎንደር ነው፤ ለእነዚያ አቡነ አረጋዊ የትግሬ ናቸው፤ ለእነዚህ ማርያም የሸዋ ናት፤ ለእነዚያ ደግሞ ሥላሴ የጎጃም ናቸው፤ ለወዲህኞቹ ሚካኤል የደቡብ ነው፤ ታቦቶቻችን ሁሉ ዘር እና ጎጥ አላቸው፡፡ ታድያ በዚህ ሁሉ አንድ ሆነን ሳለን እንዴት ተለያይተዋል እንባላለን፡፡ ይህንን የሚሉን የኛን ክፉ የሚመኙ ብቻ ናቸው፡፡
ፕሮቴስታንቶቹስ ቢሆኑ እዚህ ጌታ የወለጋ ነው፤ እዚያ የአማራ ነው፤ ወዲያ የትግራይ ነው፤ እልፍ ሲል የወላይታ ነው፤ ሲመለስ የሲዳማ ነው፤ ታድያ ሁላችንም ቢሆን ጌታን እንደ የብሔረሰባችን ተቀብለነዋል፤ ደግሞም ሁላችንም በብሔረሰባችን ቋንቋ ብቻ በመዘመር እና በመስበክ እናምናለን፤ ሁላችንም ጌታ ከኛ ቋንቋ ውጭ አይሰማም ብለን እናምናለን፤ ሁላችንም ፓስተሮቻችን ሲጣሉ ለሁለት ተከፍሎ የየራሳቸው ቸርች በመመሥረት እናምናለን፤ ሁላችንም ሌላውን ወንጌል ያልገባው መሆኑን አጥብቀን እንመሰክራለን፤ ታድያ ይህንን የመሰለ አንድነት እያለን እንዴት ተለያይተዋል እንባላለን፡፡
ሙስሊሞችና ክርስቲያኖችስ ቢሆኑ መች ተለያዩ፡፡ ይኼ የጠላት ወሬ ነው፡፡ እነዚያ ሀገሪቱን በመስጊድ በማጥለቅለቅ፤ እነዚህም በቤተ ክርስቲያን በማጥለቅለቅ ያምናሉ፡፡ እነዚያም በኃይለኛ ማይክራፎን አዛኑን በመልቀቅ፣ እነዚህም ቅዳሴውን በኃይለኛ ማይክራፎን በማሰማት ያምናሉ፡፡ ሁለቱም ከመወያየት ይልቅ መፋጠጥን፣ መልስ መሰጣጣትን ይመርጣሉ፡፡ ሁለቱም ከጥራት ይልቅ ለቁጥር ይጨነቃሉ፡፡ ሁለቱም ለአምላካቸው በመታየት ሳይሆን ለሕዝብ በመታየት ይስማማሉ፡፡ ታድያ ይህንን የመሰለ አንድነት እያለ ምኑን ተለያየነው፡፡
ምሁሮቻችን ያላቸው አንድነት የሚገርም ነው፡፡ ሕዝብ በሚያውቀው ቋንቋ ባለመጻፍ፤ በውጭ ሀገር እንጂ በሀገር ውስጥ የጥናት ወረቀት ባለማሳተም፤ በአካዳሚያዊ ክበቡ ውስጥ እንጂ በሕዝቡ ዘንድ ባለመታወቅ፤ በወረቀት እንጂ በሥራ ባለማመን፤ ከአባትነት ይልቅ በገዥነት መንፈስ በመመራት፤ ከመመሰጋገን ይልቅ በመተቻቸት በማመን፤ ምሁራዊ ዘረኛነትን በማስፋፋት፤ ምሁሮቻችን አንድ አይደሉ እንዴ፡፡ ማን ነው በመካከላቸው መለያየት አለ እያለ ያላየውን የሚያወራ፡፡ ወሬኛ፡፡
አንድነት ሰለቸን፡፡ እስኪ ደግሞ እንለያይ፡፡ የተለያየ አመለካከት፣ የዕውቀት ደረጃ፤ የአሠራር መንገድ፤ የችግር አፈታት መንገድ፤ የዕድገት መንገድ፤ የመረጃ መንገድ እስኪ ይኑረን፡፡ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአመጋገብ ብቻ ሳይሆን በሌላውም እስኪ እንለያይ፡፡ የተለያየ የፊልም ስክሪፕት፣ የተለያዩ ተዋንያን፣ የተለየ የፊልም ጭብጥ፣ የተለየ እመርታ ያለው ፊልም እስኪ ይኑረን፡፡ አንድ ዓይነት ፊልም ሰለቸን፡፡
እስኪ የተለየ ልቦለድ እንጻፍ፡፡ መቼት፣ ትረካ፣ ግጭት፣ ዐጽመ ታሪክ፣ አላባውያን፣ ገጸ ባሕርያት ከሚለው የተለየ የለም እንዴ? እስኪ እንለያይ እነዚህ የሌሉት ወይንም ደግሞ ሌሎች ነገሮች ያሉት ልቦለድ መጻፍ አይቻልም እንዴ?
አንድነት አልጠቀመንም፡፡ ዓለም የተጠቀመው ተለያይቶ ነው፡፡ ፓርላማው ይለያይ፤ ካቢኔው ይለያይ፤ሲኖዶሶ ይለያይ፤ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ ይለያይ፤ የወጣት፣ የሴት ማኅበራቱ ይለያዩ፡፡ የሞያ ማኅበራቱ ይለያዩ፡፡ በውስጣቸው ያሉ አባላቱ የተለያየ ሃሳብ፣ አመለካከት፣ አቅጣጫ፣ የዕውቀት ስብጥር፣ ዳራ፣ ይኑራቸው፡፡ይፋጩ፡፡ ተፋጭተው ተፋጭተው እንደ ብረት ተስለው የሰላ ሃሳብ ያውጡ፡፡ ምሁራኑም ይለያዩ ስለ አንድ ጉዳይ ከተለያየ አቅጣጫ ይናገሩ፣ ይጻፉ፣ ይተቹ፣ ያበጥሩ፣ ያንጠርጥሩ፡፡ አዳዲስ አካሄድ ያሳዩ፡፡ አይስማሙ፤ መስማማት የግድ አይጠበቅባቸውም፡፡ እንዲያውም ይለያዩ፡፡ የተለያየ መረጃ፣ የተለያየ ዘዴ፣ የተለያየ ግኝት ነው የምንፈልገው፡፡
የእምነት ተቋማቱም ይለያዩ፡፡ በአሠራር፣ በችግር አፈታት፣ በማስተማርያ መንገድ፣ በምእመናን አያያዝ፣ ለሀገር በሚያበረክቱት አስተዋጽዖ፤ በአሠራር ማሻሻያ፣ በመሪዎች አመራረጥ፣ ሙስናን እና ብኩንነትን በመዋጊያ መንገድ፣ በግልጽነት እና ተጠያቂነት ማስፈኛ መንገዶች ይለያዩ፡፡ ይበላለጡ፤ ይቀዳደሙ፡፡ ያን ጊዜ አንዱ ከሌላው ሃይማኖት ባይማርም አሠራር ይማራል፤ ጥበብ ይማራል፡፡ እንደ ኮካ ኮላ ጠርሙስ አንድ ከመሆን አምላክ ይታደጋቸው፡፡
እስካሁን አንድ ሆነን አይተነዋል፡፡ እስኪ ደግሞ ተለያይተን እንሞክረው፡፡ አንድነት ኃይል ነው የሚለው ይቀየርና ልዩነት ኃይል ነው ብለን እንነሣ፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ